የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እውቀትን ለማሳደግ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለጸ

የህብረተሰቡን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እውቀትን ለማሳደግ ከዝቅተኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናልዝምና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ምሁር የሆኑት ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ተናግረዋል፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶክተር ጌታቸው እንደገለጹት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩት የሀሰት መረጃዎች ለግጭቶችና ረብሻዎች በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ እና በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ስጋት መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

መደበኛ የሆኑት የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን በፍጥነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ አለማድረጋቸው ህብረተሰቡን አማራጭ የመረጃ ምንጮችን እንዲቃርም ምክንያት እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡

ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀትም ህብረተሰቡ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎችን አጠቃቀም ዕውቀቱን እንዲያሳድግ ከዝቅተኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርት ሊሰጥ ይገባል ያሉት ምሁሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መረጃዎችን ከተለያዩ ምንጮች ለማግኘት እንደሚጥሩም ገልጸዋል ፡፡