በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙና ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በልማት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱ ዜጎች ተገቢው ካሳ ስላልተሠጣቸው ለችግር መዳረጋቸውን ገለጹ ።
ዋልታ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በልማት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱ ዜጎች እንደገለጹት መንግሥት ከይዞታቸው ሲነሱ በካሬ ሜትር አነስተኛ የካሳ ገንዘብ የሠጣቸው በመሆኑ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል ።
በአዲስ አበባና ዙሪያ በልማት የተነሱት ዜጎቹ ከ 2005 ዓም ጀምሮ ለእርሻ መሬታቸው 18 ብር ፣ለግጦሽ መሬት ደግሞ በካሬ ሜትር 11 ብር ተሰልቶ የተሠጣቸው በመሆኑ ኑሯቸውን ለመምራት አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮባቸው እንደቆየ አስተያየታቸውን ገልጸዋል ።
የልማት ተነሺዎቹ መንግስት የካሳ ሁኔታውን መልሶ በማየትም ይህን ጉዳይ ፈትሾ መፍትሄ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል ።
የአዲስ አበባ አስተዳር ከንቲባ ሰሞኑን ከልማት ተነሺዎች ጋር ባደረጉት ውይይትም በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የሚገኙ የልማት ተነሺዎች ካሳን በተመለከተ ተመሳሳይ ቅሬታዎችንም ማቅረባቸው ይታወሳል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ባደረጉት ግብዣም በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አካላት በተለይ በኩዩ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቦታ አካባቢ በመገኘት ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን ዜጎች ጎብኝተዋል ።