በማዕከላዊ ጎንደር ጠገዴ ወረዳ የተቀበረ ቦንብ ፈንድቶ ሁለት ተማሪዎች ሞቱ

በማዕከላዊ ጎንደር ጠገዴ ወረዳ ቡሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አቅራቢያ የተቀበረ የእጅ ቦንብ ትናንት ፈንድቶ ሁለት ተማሪዎች ሲሞቱ ሌሎች ስድስት ተማሪዎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር እንየው ዘውዴ  እንደተናገሩት አደጋው ሊደርስ የቻለው ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውጪ 350 ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ የዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብለው ሲያጠኑ በነበረበት ወቅት ነው፡፡

“የፈነዳው ኤፍ ዋን የተባለው የእጅ ቦንብ በመሬት ውስጥ ተቀብሮ ከቆየ ረጅም አመታት ያስቆጠረ ነው” ያሉት ሃላፊው እንዴት ሊፈነዳ እንደቻለ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፍንዳታው ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ሁለቱ ህክምና ሳይደርሱ በመንገድ ላይ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሌሎች ስድስት ተማሪዎች ደግሞ በሳንጃ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ፖሊስ የአደጋውን ዝርዝር መረጃ ካጠናቀረ በኋላ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ኮማንደሩ አስታውቀዋል፡፡(ኢዜአ)