ከኢትዮጵያ ድህነትንና ረሃብን ጨርሶ የማጥፋት ስትራቴጂካዊ ጥናት ግምገማ መድረክ ተካሄደ

ከኢትዮጵያ ድህነትንና ረሃብን ጨርሶ የማጥፋት ስትራቴጂካዊ ጥናት ግምገማና ምክክር መድረክ ተካሄደ ፡፡

የስትራቴጂካዊ ግምገማ ጥናት የመጀመሪያ ዙር የምክክር መድረክ በዛሬው ዕለት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ማዕከል የተካሄደ ሲሆን ጥናቱን የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመሆን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ጥናቱ ኢትዮጵያ እኤአ በ2030 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት እንድትችል የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለድርሻ አካላት ተሣትፎና ድጋፍን በሚመለከት መሥራት የሚገባቸው ጉዳዮችን በግልጽ ለመጠቆምና ተገቢው ርብርብ እንዲካሄድ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የጥናቱ ዓላማም በኢትዮጵያ ድህነትንና ረሃብን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ እንቅፋት የሆኑ ምክንያቶችን፣ ተግዳሮቶችንና የፖሊሲም ሆነ የአቅም እንዲሁም የፕሮግራም ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣትና ችግሮቹን ለመፍታት የመፍትሔ ሃሳቦችን በመጠቆም የክትትልና የድርጊት መርሃግብር ለማዘጋጀት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ጥናቱ በዋናነት በግብርና፤ የአመጋገብና የምግብ ዋስትና፣ ድህነት፣ ማህበራዊ ጥበቃ እና የአስቸኳይ ጊዜ ዝግጁነትና የአደጋ መከላከል አስተዳደር ላይ ያተኮረውን ጥናት ለማካሄድ የምርምር ተቋምና ሴክሬቴሪያት ሆኖ መሰየሙ ተገልጿል፡፡

የስትራቴጂካዊ ጥናቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ከዚህ በፊት የተዘጋጁ አበይት ጥናቶችን በመገምገም፣ በማጠናከርና በማቀናጀት ከተለያዩ የፌደራል መንግስት ተቋማትን በማሳተፍ እየተካሄደ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በዛሬው የምክክር መድረክ ላይም ከፌደራል የመንግስት መሥሪያ ቤቶች፣ ከአካዳሚክ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ከምክክር መድረኩ በሚገኘው ውጤት መሠረት የሚዘጋጀው የመጨረሻ ሪፖርት ለኢፌዴሪ መንግስት የሚቀርብ ሲሆን በከፍተኛ የአመራር ደረጃ በሚካሄደው የፌደራል መንግስት መሥሪያ ቤቶች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች አካላት በሚሳተፉበት መድረክ ፀድቆ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡