አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ በአግባቡ ለማስፋት የሚያስችል ጽህፈት ቤት በትምህርት ሚኒስቴር ሥር መቋቋሙን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት በአጠቃላይ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሥራውን ለማሻሻል የሚያስችለውን መነሻ ለጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት እንዲቀርብ ተደርጎ ፀድቋል ።
በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ውይይቶች ተካሄደው የተጨመቀው ሓሳብ መዘጋጀቱንም ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በመግለጫው ተናግረዋል ።
ፍኖተ ካርታው በተመለከተ በተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር የውይይት መድረክም 700ሺህ ያህል ሰዎችም ታሳታፊዎች መሆናቸውም ተገልጿል ።
በፍኖተ ካርታው ውይይት ወቅት የአንድ ዜጋ የትምህርት መጀመሪያ ዕድሜ 6 ወይም 7 እድሜ ይሁን በሚል የትኩረት ሓሳብ ላይ ውይይት የተደረገ መሆኑ የገለጹት ዶክተር ጥላዬ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የሚያስችለው ትምህርት እስከ 10ኛ ወይም 12ኛ ድረስ ይሠጥ የሚለው ሌላው መከራከሪያ ነጥብ እንደነበር ገልጸዋል ።
በአገሪቱ ካለው የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ተደራሽነት አንጻር የህጻናት ትምህርት መጀመሪያ ዕድሜ 7 ቢሆን እንዲሁም ዩኒቨርስቲ ለመግባት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ማጠናቀቅ ጠቃሚ እንሚሆንም በትምህርት ፍኖተ ካርታው በጉልህ የተነሱ ሓሳቦች መሆናቸውንም ዶክተር ጥላዬ ገልጸዋል ።
የመማር ማስተማር ሂደቱን በተመለከተ ከውጭ የሚቀመሩ የትምህርት ፖሊሲዎች እንዳሉ የጠቀሱት ዶክተር ጥላዬ አገር በቀል እውቀቶች በስፋት በመማር ማስተማሩ ላይ ተግባራዊ እንዲደረጉ በፍኖተ ካርታ ውይይቱ ተጠይቋል ።
በተጨማሪም ተማሪዎች እስከ 12ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ በዩኒቨርስቲ በሚገቡበት ወቅት የመጀመሪያ ዓመትም የአገራቸውን ታሪክ እንዲማሩ የሚደረግ መሆኑም በፍኖተ ካርታው መድረግ ላይ የተነሳ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል ።
በአጠቃላይ በአገሪቱ በመጀመሪያ ደረጃ ፣ ሁለተኛ ደረጃ ፣ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ መምህራንም ደረጃ የሚያስቀምጥ አዲስ አሠራር በፍኖተ ካርታው ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል ።
እስካሁን ድረስ በትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ በተደረገው ውይይትም የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ተሳታፊነት የተካሄደ መሆኑንና መንግሥት እስከ አርብቶ አደርና አርሶአደሩ ድረሰ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሊወያዩበት ይገባል የሚል አቋም እንዳለውም ሚኒስትሩ ገልጸዋል ።
በትምህርት ፍኖተ ካርታ ዙሪያ በመላ አገሪቱ ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚቀጥለው ሳምንት በፍኖተ ካርታው ላይ ውይይት እንዲያደርጉ ዝግጅቶች የተጠናቀቁ ሲሆን ለዚሁም ተግባር ከፌደራልና ክልል ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል ።
የትምህርት ፍኖተ ካርታው ስኬታማ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል ።