የኢህአዴግ ምክር ቤት በቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ

የኢህአዴግ ምክር ቤት ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ ከወታደርነት እስከ ርዕሰ ብሄርነት ሀገራቸውና ህዝባቸው የሠጧቸውን ኃላፊነት በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት በተወጡት የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለፀ።

የቀድሞ ፕሬዚዳንታችን በፖለቲካና አስተዳደራዊ መስኮች በሀገራችን ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማኖር የቻሉና ለአዲሱ ትውልድ መልካም ምግባሮችን ትተው ያለፉ መሪ ናቸው።

ከባለሙያነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት ባገለገሉባቸው የሥራ መስኮች አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችን በፅናት በማለፍ ለስኬት የበቁ ናቸው።

በሁለት የመንግስት አስተዳደሮች ወቅት በነበራቸው የህዝብ እንደራሴነት ውክልናም ለህዝቦች ሰላምና ለሀገር እድገት አበክረው ሰርተዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሀገራችንን ለ12 አመታት በታታሪነትና በቅንነት ርዕሰ ብሄር ሆነው ያገለገሉ የሀገራችን ባለውለታም ናቸው።

እርሳቸውን ስናስብ ከመንግስት አስተዳደር ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃና በበጎ  አድራጎት ተግባራት የነበራቸውን አኩሪ ገድል አብረን እንዘክራለን።

የኢህአዴግ ምክር ቤት በእኝህ ታላቅ መሪ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን ሲገልፅ የአሁኑ ትውልድ መልካም አርዓያቸውን በመሰነቅ ለግላዊ ስኬት ብሎም ለሀገር ሰላምና እድገት እንደሚያውለው በመተማመን ነው።

በዚሁ አጋጣሚ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች መጽናናትን እንመኛለን።(ኢዜአ)