ከአሶሳ ወደ ቶንጎ ይጓዝ በነበረ ሚኒባስ ላይ በደረሰ የፈንጂ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተገለጸ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሶሳ ወደ ቶንጎ ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ተሸከርካሪ ላይ በደረሰ የፈንጂ አደጋ የአስር ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሃሩን እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ዛሬ ጠዋት 18 ሰዎችን አሳፍሮ ከአሶሳ ወደ ቶንጎ ይዞ ይጓዝ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ቤጊ መገንጠያ የተባለበት ስፍራ ሲደርስ በፈንጂ በደረሰበት አደጋ ነው፡፡

በአደጋው በተሸከርካሪው ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ የ10 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን አስታውቀዋል፡፡

ሌሎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች ደግሞ ቤጊ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተው የአደጋው መንስኤ ለመለየት ምርመራ መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡ (ኢዜአ)