የወሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ሰላም ለማረጋገጥ እየሠሩ መሆኑን ገለጹ

የወሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ሰላምን ለማረጋገጥ በየጊዜው  የተለያዩ  ሥራዎችን  እንደሚያከናውኑ ገለጹ ።

የወሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለዋልታ ቴሌቭዠን በሠጡት አስተያየት እንደገለጹት በሌሎች የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ችግሮች ሲፈጠሩ በወሎ ዩኒቨርስቲ ዘላቂ ሰላም መፍጠር የተቻለው በተለያዩ  አደረጃጀቶች በጋራ መሥራት በመቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

በዩኒቨርስቲው  ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የተማሪዎች ፖሊሶችን በመምረጥ ከተማሪዎች ህብረት  ጋር  በጋራ በመሥራት እስከዛሬ  ድረስ  ምንም አይነት  ችግር እንዳይከሰት ትልቅ  አስተዋጽኦ ማበርከቱን  ተማሪዎቹ ገልጸዋል ።

ከዩኒቨርስቲው የትምህርት ማህበረሰብ በተጨማሪም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን  ሰላምን ለማስጠበቅ በጋራ የሚያከናውኑት ሥራም  ለተገኘው  ውጤት  በምክንያት  የሚጠቀስ ተግባር  መሆኑን ገልጸዋል ።

የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በሠጡት አስተያየት ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የወሎ ዩኒቨርስቲን ተሞክሮ  በመውሰድ  የዩኒቨርስቲያቸውን ሰላም  ማረጋገጥ  እንደሚችሉም  ጠቁመዋል።

የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር በለጠ ጌታሁን በበኩላቸው እሳቸውን ጨምሮ  የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ኃላፊዎች  ፕሮግራም በማውጣት 24 ሰዓት ከተማሪዎቹ ጋር ጥምረት  በመፍጠር  ሥራዎች  እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል  ። 

ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ጥቃቅን ችግሮችን በመፍታትና በዩኒቨርስቲው ችግሮች  እንዳይከሰቱም  ጥምረቱ ትልቀ እገዛን አድርጓል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ።

በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ አመራሮችም የወሎ ዩኒቨርስቲን ተሞክሮ በመውሰድ ተመሳሳይ  ውጤት  ማስመዝገብ  ይችላሉ ብለዋል ።