የሀገር ውስጥ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የአገልግሎት አሠጣጥ የህግ ማዕቀፍና የአፈጻጸም ክፍተት አለባቸው ተባለ

የሀገር ውስጥ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የአገልግሎት አሰጣጥ የህግ ማዕቀፍና የአፈጻጸም ክፍተት እንደሚስተዋልበት ተገልጿል፡፡

የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሀገር ውስጥ የስራ ስምሪት አገልግሎት አሰጣጥ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚዳስስ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የአገልግሎት አሰጣጡን በሚመለከት የጥናት ውጤት የቀረበ ሲሆን በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትም የተጠናከር ስራ ሊከናወን እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

በመንግስት ደረጃ ሲሰጥ የቆየው ይህ ተግባር በግሉ ዘርፍ መከናወኑ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ አጋዥ እንደሆነ የጠቆሙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒሰትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ስራው በተሟላ የህግ ማዕቀፍ ባለመከናወኑ በህብረተሰቡ ዘንድ ቅራኔ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡ የህግ ማዕቀፍና የአፈጻጸም ክፍተት እንደተስተዋለበት የገለጹት ጥናት አቅራቢዎች ክፍተቶቹን ለመቅረፍ አስፈላጊው የህግ ማዕቀፍ ሊዘረጋ እና የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲዎች በበኩላቸው የአገልግሎት አሠጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ መንግስት በህገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው ገልጸው ከጨረታ ጀምሮ እስከ ኤጀንሲዎች ድርሻ ድረስ ያለውን የዋጋ ተመን ሊያስቀምጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የሀገር ውስጥ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተነሱ የህግ ማዕቀፍና የአፈጻጸም ክፍተቶችን ለመቅረፍና የተሻለ አደረጃጀት ለመዘርጋት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ኤጀንሲዎቹ ህግና ስርአትን ተከትለው እንዲሰሩ ያሳሰቡ ሲሆን የተነሱ የህግ ማዕቀፍና አደረጃጀት ክፍተት ለመቅረፍ መሥሪያ ቤቱ በ100 ቀናት ዕቅድ ውስጥ አካቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡