ለሁለት ወራት የጤና አገልግሎት የሚሰጥ የሀኪሞች ቡድን ወደ ኤርትራ ተላከ

ለሁለት ወራት የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ የሀኪሞች ቡድን ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ መላካቸው ተገለጸ፡፡

ወደ ኤርትራ በመሄድ የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው የህክምና ቡድኑ 35 ጠቅላላ ሀኪሞችና አራት እስፔሻሊስቶችን ያካተተ እንደሆነ ታውቋል፡፡

የህክምና ቡድኑን የሚመሩት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ የሀኪሞቹ ጉዞ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ መካከል ያለውን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የህክምና ባለሙያዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር የሚጫወቱት ሚና እጅግ የጎላ እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትር ደኤታዋ በቀጣይም ወደ ሌሎች የምስራቃ አፍሪካ ሀገሮች መሰል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ሀብታሙ ወረታው እና ዶክተር ማህሌት አንበሴ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በጠቅላላ ሀኪምነት የተመረቁ የህክምና ባለሙያዎች ሲሆኑ ወደ ኤርትራ በመሄድ በህክምና ሙያ ህዝቡን ለማገልገል በመታደላቸው ታላቅ ደስታና ክብር ይሰማናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሀኪሞች በኤርተራ በሚያደርጉት የሁለት ወራት ቆይታ በዋነኝነት በህክምና ሙያቸው ህዝቡን ማገልገል፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግና ህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር በኩል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት እንደሚያከናውኑም ገልፀዋል፡፡ (ምንጭ፡-የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)