የጣርማ በር -ሞላሌ-ወገሬ የመንገድ ግንባታ ሥራ በይፋ ተጀመረ

118 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጣርማ በር-መለያያ-ሰፌድ ሜዳ -ሞላሌ-ወገሬ የመንገድ ግንባታ የፕሮጀክት ሥራ በይፋ ተጀመረ።

የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆነው የመንገድ ግንባታው ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ የሚደረግበት ሲሆን፥ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃም ነው ግንባታው የሚከናወነው።

የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የመንገድ ግንባታውን በይፋ አስጀምረዋል።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን የመንገድ ግንባታውን የሚያከናውን ሲሆን፥ ክላሲክ ኮንሰልቲንግ በአማካሪ ድርጅትነት ይሳተፋል።

በአጠቃላይም በ36 ወራት ውስጥ የመንገዱን ግንባታ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው መንገዱ ከአዲስ አበባ 180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ጣርማበር ዋሻ አካባቢ ተነስቶ ሞላሌ ሲደርስ በመታጠፍ ወገሬ ላይ ያበቃል።

ግንባታው ሲጠናቀቅም በአካባቢው በስፋት የሚመረቱ ምስር፣ ተልባ፣ አተርና ቅቤ ምርቶች እንዲሁም  የቁም ከብቶችን ወደ ገበያ በቀላሉ ለማቅረብ እንደሚያስችል ተመልክቷል።

በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኘውን የኮባልት ማዕድን ምርት ጥቅም ላይ ለማዋልም እንደሚያስችልም ነው የተገለፀው።