የአጋሮ ከተማ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ግንባታን ለማፋጠን የከተማው አስተዳደር እየሠራ ነው

የአጋሮ ከተማን የ10ነጥብ1 የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ግንባታን በተያዘለት የጊዜ  ገደብ ለማጠናቀቅ  የአጋሮ ከተማ  አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን  አስታወቀ ።

የአጋሮ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚፍታህ አብደላ ለዋልታ እንደገለጹት የአጋሮ ከተማ አስተዳደር ከኦሮሚያ  ክልል  መንግሥት  ጋር በመተባባር በ420 ሚሊዮን ብር ግንባታው እየተከናወነ ያለውን የከተማውን የውስጥ ለውስጥ መንገድ  ግንባታ ለማፋጠንም እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የከተማውን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታን ለማፋጠን  ችግር የሆኑትን  የወሰን ማስከበር፣ የካሳ ክፍያና የዲዛይን ሥራዎችን  ቀድሞ ለማጠናቀቅም ከክልሉ መንግሥት ጋር  በመናበብ እየተሠራ መሆኑን  አቶ ሚፍታህ ተናግረዋል ።

የአጋሮ ከተማ  ነዋሪ የሆኑት መምህር ያደታ አያና ለዋልታ እንደገለጹት የአጋሮ ከተማ  ቀደም ብሎ ከተቆረቆሩት ከተሞች አንዷ ብትሆንም የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ ወደ  ኋላ  በመቅረቷ አሁን የተጀመረው ግንባታ ትልቅ  ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል ።

የከተማው ነባር  ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ነዝሬ አባፎጊ በበኩላቸው የአጋሮ ከተማ  የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ አዲስ  ተስፋን  ሰንቆ የመጣ መሆኑንና  ህብረተሰቡ   ከ20 ዓመት በላይ ሲያነሳው የነበረው  የመንገድ ይገንባልን ጥያቄው ምላሽ በማግኘቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ።