ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያን ጎበኙ

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አውጉስታ አካባቢ የሚገኘውን ሐምሊ ፊስቱላ ኢትዮጵያን ጎበኙ፡፡

ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣት ኢትዮጵያዊያንን በማከም ከፊስቱላ ህመም መፈወስ የቻለ አንጋፋ ድርጅት መሆኑን ፕሬዝዳንቷ በጉብኝታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ድርጅቱ ንፁህና ሳቢ ተቋም መስርቶ ከሚሰጠው ዘመናዊ ህክምና ባለፈ አዋላጅ ነርሶችን በብቃት እያሰለጠነ ለሌሎች የህክምና ተቋማት ጭምር ከፍተኛ ደጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኝ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለውለታ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የድርጅቱ መስራች የዶክተር ካትሪን ሐምሊን 95ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው የተከበረ ሲሆን የሥነ-ሥርዓቱ ታዳሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ የገለፁት ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ቀጣይ ጊዜያቸው መልካም እንዲሆን ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ (ምንጭ፡-የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት)