የአየር ንብረት ለዉጥ ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን ይጎዳል ተባለ

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ቀያቸውን ለቀው ከሚሰደዱ ሰዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ይላል የተባበሩት መንግስታት ይፋ ያደረገው ጥናት፡፡

ሴቶች የቤተሰባቸው የእንክካቤ ማእከል በመሆናቸው የአየር ንብረት ለውጥ  በሚያከትላቸው የጎርፍ እና ድርቅ ክስተት ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ለችግር ተጋላጭ ይሆናሉ ይላል ጥናቱ፡፡

እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2015 ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተስማማበት የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት በሴቶች ላይ የሚደርሰው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ተመጣጣኝ ስላልሆነ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲጠናከር የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን መካተታቸው አይዘነጋም፡፡

ለአብነት እንኳ በማዕከላዊ አፍሪካ የሚገኘው የቻድ ሐይቅ 90 በመቶ ገደማ በመጥፋቱ ሳቢያ በአካባቢው የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ለአደጋ ተጋልጠዋል፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ ሴቶች በተለየ መልኩ ተጎጂ ሆነዋል፡፡ ለዚህ ምክኒያቱ ደግሞ በባሕሩ ዳርቻ የሚገኘው ውሀ እየቀነሰ በመሄዱ ሴቶች ውሃን ለማምጣት ብዙ መጓዝ ግድ ብሏቸዋል፡፡

በበጋ ወራት የአከባቢው ወንዶች ማህበረሰባቸውን የመንከባከብ ስራን ለሴቶች ትተው ወደ ከተሞች ይሄዳሉ ስትል የቻድ ተወላጅ ሴቶች እና ህዝቦች ማህበር አስተባባሪ ሂንዱ ኦሙራ ኢብራሂም ትናገራለች፡፡

አሁን ላይ የበጋው ወቅት ረዥም በመሆኑ ቤተሰብን የመንከባከቡ እና የመመገብ ስራ በሴቶች ጫንቃ ላይ ይወድቃል ስትል ሂንዱ ኦሙራ ለቢቢሲ ተናግራለች፡፡

የዚህ ችግር ሰለባዎች በገጠር የሚኖሩ ሴቶች ብቻ አይደሉም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ድህነት ውስጥ ስለሚገኙ ከወንዶች ያነሰ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ላይ እንደሚገኙ ይስተዋላል፡፡ ይህም በመሠረተ ልማት; በሥራ እና በቤት ውስጥ ከሚደርሱ አደጋዎች ለማገገም ያለውን ሂደት አስቸጋሪ ያደርገዋል::

እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2005 በአሜሪካዋ ሉዚያና ካትሪና ተብሎ በተጠራው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በደረሰው የጎርፍ አደጋ በጣም የተጎዱት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ አፍሪካ አሜሪካዊ ሴቶች ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በኒው ኦርሊየንስ ውስጥ ካትሪና ከመከሰቱ በፊትም  የአፍሪካ አሜሪካውያን ህዝቦች  ከፍተኛ ድህነት ውስጥ ነበሩ የሚሉት የሩተርስ ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና የፆታ ጥናቶች ፕሮፌሰር ጃክሊን ሊት ናቸው፡፡

እንደ ፕሮፌሰሯ ገለጻ በከተማዋ በደህነት ውስጥ ከሚኖሩት ቤተሰቦች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ልጆቻቸውን ብቻቸውን ያለአባት የሚያሳድጉ እናቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ቤተሰቦች የዕለት ተዕለት ኑሮዋቸውን ለማሸነፍ እና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጠናከር የእርስ በርስ የማኅበረሰብ አውታሮች ላይ መሰረታቸውን ያደርጋሉ፡፡ አደጋው በመከሰቱ የማህበረሰቡን ማህበራዊ አውታሮች ከመበጣጠሱም ባለፈ ሴቶችን እና ህጻናትን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጧል፡፡

አደጋዎች በተከሰቱ ወቅት ጾታዊ ጥቃቶች በሴቶች ላይ የሚፈጸመው የኃይል ድርጊት እንደሚጨምር የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በሲሪላንካ፤ በኢንዶኔዥያ እና ሕንድ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2004 በተከሰተ ሱናሚ የተጎዱ ሴቶች ከወንዶች ይበልጣል፡፡ በሕይወት የተረፉት ወንዶች ቁጥር ከሴቶች ሲታይ በ3 እጥፍ ይበልጣል ይላል ኦክስፋም ይፋ ያደረገው ሪፖርት፡፡

ከ20 አመት በላይ የተካሄደ ሌላ ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ የተከሰቱ አደጋዎች የሴቶችን አማካይ የእድሜ ጣራ ከወንዶች ያነሰ እንዲሆን አድርጎል፡፡

የሴቶች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው በዳበረባቸው ሀገሮች ውስጥ ግን የእድሜ ጣራ ልዩነቱ አነስተኛ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

በዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ድርድር ውስጥ የሚገኙ ሴቶች አማካይ ውክልና ከ30 በመቶ በታች ነው::

ከዓለም ህዝብ ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡ ህይወታቸው ላይ ተጽእኖ በሚያሳርፉ ውሳኔዎች ውስጥ ልንሳተፍ ይገባል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ለስልጣን የሚደረግ ውጊያ አይደለም፡፡ በህይወት ለመኖር የሚደረግ ትግል እንጂ፡፡ ሴቶች ከዚህ አንጻር ድምጻችን እንዲሰማ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ትላለች ሂንዱ ኦሙሩ ኢብራሂም፡፡

የዝግጅት ክፍላችንም የሴቶች ቀን በአመት አንዴ ከመዘከር ባለፈ በየእለት ተእለት ተግባራቸው ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከማወደስ በተጨማሪ ህይወታቸውን በሚፈታተኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዩች ላይ ተሰሚኒታቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ሊደገፉ ይገባል ይላል፡፡