በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ሰንደቅ አላማቸውን ዝቅ በማድረግ ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው

መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ሰንደቅ አላማቸውን ዝቅ በማድረግ የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

በትናንትናው ዕለት ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ሲበር የነበረና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ተከስክሶ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኢምባሲዎች ሰንደቅ አላማቸውን ዝቅ በማድረግ ሀዘናቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ህይወታቸውን ላጡ የካናዳና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን በመመኘት አስፈላጊውን ትብብርና እርዳታ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም ኤምባሲው የሀገሪቱን ሰንደቅ አላማ ዝቅ በማድረግ ሀዘኑን በመግለፅ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የብሪታኒያ ኤምባሲ በበኩሉ በተከሰተው አደጋ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን በመመኘት የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማም ዝቅ ብሎ እንዲሰቀል አድርጓል።

በኢትዮጵያ የጀረመን፣ የሩሲያ፣ የስዊድን፣ የህንድ እና የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችም በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ በአደጋው ህይዎታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በሙሉ መፅናናትን ተመኝተዋል።