በቻይና ዕፅ በማዘዋወር ተጠርጥራ በእስር ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያዊት ጉዳይ መንግስት በቅርበት እየተከታተለው ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

መንግስት በቻይና እፅ በማዘዋወር ተጠርጥራ እስር ላይ የምትገኘውን ናዝራዊት አበራን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ መንግስት ጓንዡ ግዛት በሚገኘው ማረሚያ ቤት የምትገኘውን የናዝራዊት አበራን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ተናግረዋል።

በስፍራው በሚገኘው የኢፌዴሪ ቆንስላ ፅህፈት ቤት ሰራተኞችም ናዝራዊት በምትገኝበት ማረሚያ ቤት ሶስት ጊዜ በመሄድ ያለችበትን ሁኔታ ተመልክተዋል ነው ያሉት።

መንግስት ሃላፊነቱን ተጠቅሞ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን አቶ ነቢያት ጠቅሰው፥ ተጠርጣሪዋን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ ከተጠረጠረችበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሞት ፍርድ ተፈርዶባታል በሚል እየተናፈሰ ያለው ወሬ ሃሰት መሆኑንም ገልጸዋል። አቃቤ ህግም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ክሱን ካቀረበ በኋላ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አምርቶ እንደሚወሰንም አስረድተዋል።

መንግስት አሁን ላይ እንደ ዜጋ መጠየቅ የሚችለውን እያደረገ ሲሆን፥ ትክክለኛ ፍርድ እንድታገኝ ክትትል ይደረጋልም ነው ያሉት።