የጤና ሚኒስቴር የመድሃኒት አቅርቦት ችግርን ለመከላከል የሚያስችል አዲስ መመሪያ ይፋ አደረገ

በማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶች ላይ ሚስተዋለውን የአሰራር ክፍተት እና የመድሃኒት አቅርቦትን ችግርን ለመከላከል የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር አዲስ መመሪያ ይፋ አደርጓል፡፡

በኢትጵያ የመድሃኒት አገልግሎቱ ጠንካራ ስርአት የሌለው በመሆኑ በርካታ ችግሮች ሲገጥሙ ይስተዋላል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም ሞዴል ማህበረሰብ መድሃኒት ቤት የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በተለይ መድሃኒት ለመግዛት ወደ መድሃኒት ቤቶች የሚሄዱ ተጠቃሚዎች የሚወስዱትን መድሃኒት አጠቃቀም በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከማድረግ አንፃር ለባለሞያዎች በቂ ስልጠና ለመስጠት መታሰቡንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባዘጋጀው መድረክ ተገልጿል፡፡

መመሪያው በአዲስ አበባ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት በክልሎች ደግሞ በአንድ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት አቶ ያእቆብ ሰማን የገለጹት፡፡

መመሪያው መድሃኒቶች ዋጋቸው ተመጣጣኝ  እና ጥራታቸውን የጠበቁ ሆነው በቅርበት መገኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡  ይህን ለማድረግ መድሃኒት ቤቶች በብዛት የማይገኙባቸው አካባቢዎችን በማጥናት በአዲስ አበባ በመንግስት ሚተዳደሩ 50 መድሃኒት ቤቶችን ለመክፈት እየተሰራ እንደሆነ  አቶ ያእቆብ አክለው ገልጸዋል፡፡

መድሃኒቶች ግዜያቸው እንዳያልፍም ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ የት እንደደረሱ የሚያመላክት የቁጥጥር ስርአት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሚሰሩበት መድሃኒት ቤቶች ከሀኪም ትእዛዝ ውጪ የሚሸጡ መድሃኒቶች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉትን ችግሮችን ከመቅረፍ አንፃር መመሪያው ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሚሰሩባቸው መድሃኒት ቤቶች ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር እና ከሀኪም ትእዛዝ ውጪ የሚሸጡ መድሃኒቶች በተያያዘ የሚስተዋሉትን ችግሮችን ከመቅረፍ አንፃር መመሪያው ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የገለጹት፡፡

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን ጥናት በተደረገባቸው የግል እና የመንግስት መድሃኒት ቤቶች በተመሳሳይ መድሃኒቶች ላይ ከ0 ነጥብ 6 እስከ 400 በመቶ የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

መመሪያው ተግባራዊ ሲደረግ አግባብ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን የሚቀንሰ ሲሆን እስከ 25 በመቶ ብቻ የዋጋ ጭማሪ መኖር እንደሚገባም ተገልጿል፡፡