ምዕመናን የትንሳኤን በዓል የተቸገሩትን በመርዳት ማክበር እንደሚገባቸው የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ

በነገው ዕለት የሚከበረውን የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ  ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የኃይማኖት አባቶች የተቸገሩትን በመርዳት በዓሉን ማክበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብርሀነ ኢየሱስ እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ ናቸው፡፡

የኃይማኖት አባቶቹ ምዕመናን ከኃይማኖቱ የተወረሱ እሴቶችንና ባህሎችን በጠበቀ መልኩ በዓሉን ሊያከብሩ እንደሚገባ በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

በዓሉን ችግረኞችንና አቅመ ደካሞችን፣ በኃዘንና በችግር ላይ ከሚገኙ ወገኖች ጎን በመሆን እንዲሁም አረጋውያንንና አሳዳጊ የሌላቸውን ሕጻናት በማሰብ ሊያከብሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ምእመናን የትንሳኤ በዓልን ማክበር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠናከር እና ሰላም እንዲሰፍን በመከባበር፣ በወንድማማችነት፣ በይቅር ባይነት እና በመተዛዘን መንፈስ ሁሉም ሊሰራ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

ግጭትን ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ የጥላቻ ንግግር እና ተግባራት እንዲቆጠቡ አባታዊ ምክራቸውንም አስተላልፈዋል፡፡