ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ አስተዋጽኦዋ ሽልማት ተበረከተላት

በግብጽ ሻርማልሼክ ከተማ በተካሄደው ስነስርዓት የአፍሪካ የሰብዓዊና ህዝቦች መብቶች ኮሚሽን፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች በማስተናገድ ሁለተኛን ደረጃ በመያዟ ሽልማት አበርክቶላታል።

በአፍሪካ የስደተኞች፣ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ እንዲሁም የውስጥ ተፈናቃይ ዜጎች ልዩ ራፖርተር ኮሚሽነር ማያ ሳሂል፣ ሥነስርዓቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች በማስተናገድ ላይ የሚገኙት ሀገራትን ለማመስገን መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ሰፊ እና ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ የስደተኛ መጠለያ ለሚገኙባቸው ሀገራት እውቅና ለመስጠት በማሰብ መዘጋጀቱንም ነው የተናገሩት።

ሽልማቱን በግብጽ የኢትዮጵያ ምክትል አምባሳደር አቶ መርዋን በድሪ ተቀብለውታል።

ምክትል አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ አፍሪካ የሚገጥሟትን ልዩ ሁኔታዎች በሚያወሳው ስምምነት የዝግጅት ወቅት ዓይነተኛ ሚና መጫወቷን ጠቅሰው፥ ስደተኞችንም በዚያው አግባብ ተቀብላ እንደምታስተናግድ ገልጸዋል።

በግጭት፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተነሳ ከሀገራቸው የተሰደዱትን አፍሪካውያን በማስተናገድ ኃላፊነታቸውን ለሚወጡት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት እውቅና በመሰጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሽልማቱ በአፍሪካ ህዝቦች ስም ለኢትዮጵያ እውቅና የሚሰጥ የምስክር ወረቀትን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል፡፡

(ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር)