ህዝበ ሙስሊሙ ከጥቃቅን ልዩነቶች ይልቅ አንድነቱን ማጠናከር አለበት- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ህዝበ ሙስሊሙ ከጥቃቅን ልዩነቶች ይልቅ አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቋማዊ ለውጥ እና የአንድነት ሀገር አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ በክቡር እንግድነት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በትናንሽ ጉዳዮች ከመሳሳብ ወጥቶ ትልቁን ህዝብ ማገልገል ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ወጣቶች ትላልቅ አሊሞችን እንዲያደምጡና አርያነታቸውን እንዲከተሉ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኛ ኢትዮጵያውን በራሳችን ውስጥ ሰላም ሳናወርድና አንድነትን ሳናረጋገግጥ ለሌሎች መከታ ልንሆን አንችልምና፤ ሙስሊሙ ማህበሰረብም በመካከሉ ያለውን ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል” ብለዋል፡፡

ይህ በዓይነቱ ትልቅና ታሪካዊ የሆነ ጉባዔ የሙስሊሙን አንድነት የሚያጠናክር አደረጃጀት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ችግሮችም መፍትሄ የሚሆኑ የውሳኔ ሃሳቦችን እንደሚያመነጭም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

ለዘመናት የተጠራቀሙ ችግሮችን በቅደም ተከተል መፍታት እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶክተር አብይ አህመድ ከጥላቻ በመውጣት ወደ ፍቅር ፊቱን መመለስ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በሙስሊሙ መካከል አክራሪና አለዛቢ ሆኖ መታየት አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቅዱስ ቁርዓን የተለያዩ ጥቅሶችን በመጠቀም የአንድነትና የሰላም ፋይዳን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አንድነት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደሚጠባበቅና ከጉባዔው ሀይማኖት የሚያፀና፣ ሀገር የሚያቀና መፍትሄ ይጠበቃል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ከጦርነት አንዳችም ነገር አናተርፍም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእስልምና ሀይማኖት የሰላም በመሆኑ ተከታዮችም ለዘላቂ ሰላም እንዲተጉ ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚጀመረውን የረመዳን ፆም ምክንያት በማድረግ ለመላው ሙስሊም ማህበረሰብ የመልካም ምኞች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥና አንድነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙብቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ በበኩላቸው ወቅቱ የፈጠረውን ሁኔታ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን ለማጠናከር እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል፡፡

እስልምና ከግጭት በመራቅ አንድነትና ሰላምን የምሰብክ እምነት ነው ያሉት ሀጂ ኡመር ይህንን አጠናክረው መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል፡፡