አለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ44ኛ ጊዜ ተከበረ

አለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ሜይዴይ "ሠላም ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሠራተኛው መደራጀትና ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት ነው" በሚል መሪ ቃል ዛሬ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡

ሰራተኞች ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ለውጥ ያላቸው ሚና የማይተካ መሆኑን ተገንዝበው ለሀገራቸው ልማት እና ሰላም የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ አጠናቅሮ መቀጠል እንዳለባቸው በበዓሉ ላይ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ሠራተኛው መብቱን፣ ጥቅሙንና የሥራ ላይ ደህንነቱን ለማስከበር ባደረገው ትግል፤ አገሪቱ በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለመራመድ የምትችልበትን ጥርጊያ ማበጀት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያ ሰራተኛ ዛሬ ሀገሪቱ ለደረሰችበት የእድገት ከፍታ ምትክ የማይገኝለት ድርሻ አበርክተዋል ነው ያሉት፡፡

የሠራተኛዉ በሠራተኛ ማህበር መደራጀት ሠራተኛውን ብቻ ሳይሆን አሠሪውንና መንግስትን ከፍ ባለ ደረጃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተናገሩት ሚኒስትሯ በበዓሉ መሪ ቃል ስለ ሠራተኛው መደራጀት የተላለፈው መልእክት ተግባራዊ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል፡፡

ግባችን በኢንዱስትሪ የበለፀገ ሀገርና ድህነትን የተሻገረ ህብረተሰብ መገንባት በመሆኑ የሥራ አያያዛችን በጋራ መግባባትና ባለቤትነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ሚኒስትሯ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የሠራተኛው መብትና ጥቅም ይበልጥ እንዲከበርና የሀገራችን ልማት እንዲፋጠን ከአጋር ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስተር ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ኤርጎጌ ገልፀዋል፡፡

የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው የዘንድሮው አለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ሲከበር የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታና የሠራተኛውን ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ገልፀው፤ የሠራተኛው መደራጀት እና ሁለንተናዊ እድገት ማምጣት የሚቻለው ሠላም ሲሰፍን በመሆኑ መንግስት እና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ካሳሁን አክለውም ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ለሠራተኛው የሙያ ደህንነትና ጤንነት፣ ተመጣጣኝ የደመወዝ ክፍያ እንዲሁም ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲኖር መንግስት፣ አሠሪዎች፣ ባለሃብቶች እና ሌሎች የኢንደስትሪውን እድገት የሚሹ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች የሠራተኞች የመደራጀት መብት፣ መነሻ የደመወዝ ወለል መወሰን እንዲሁም የሀገር ውስጥ አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አሠራር መፈተሽ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት ::

እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ አለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ሜይዴይ ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ130ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ44ኛ ጊዜ ነው የተከበረው፡፡