የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብር ሥነስርዓት በመጪው እሁድ ይፈፀማል

የኢፌዴሪ ቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብር ሥነስርዓት የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚፈፀም ተገለፀ።

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ብሄራዊ የቀብር አስፈፃሚ ኮሚቴ በዛሬው እለት የቀብር ሥነስርዓቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያና የቀብር ስነ ስርዓቱን አስመልክተው ነው መግለጫ የሰጡት።

በመግለጫውም የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስከሬን የፊታችን ቅዳሜ ማለትም ሚያዝያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ከጀርመን አዲስ አበባ እንደሚገባ ተመልክቷል።

የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 27/2011 ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮም በሚሊኒየም አዳራሽ የሽኝት መርሃ ግብር እንደሚካሄድ፣ ቀጥሎም የቀብር ስነ ስርዓታቸው ከቀኑ በ9 ሰዓት በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈፀምም ነው የተገለፀው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው ስብሰባውም ለኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ መላኩን ኮሚቴው ገልጿል።

በተያያዘ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈትን በማስመልከት የሀዘን መግለጫ የክብር መዝገብ አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የሀዘን መግለጫ የክብር መዝገቡ ዛሬ እና ነገ ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚውልም ነው የተገለፀው።

(ምንጭ፡-ኤፍቢሲ)