የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አስከሬን በሚሌኒየም አዳራሽ ስንብት እየተደረገለት ነው

የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስክሪን በሚሌኒየም አዳራሽ ስንብት እየተደረገ ነው፡፡

በከፍተኛ ክብር ታጅቦ ቦሌ በሚገኘው የሚሌኒየም አዳራሽ የደረሰው የቀድሞው ፕሬዝዳንት አስክሬን በተለያዩ ዝግጅቶች ስንብት እየተደረገለት ነው የሚገኘው፡፡

አስከሬኑ በሚሌኒየም አዳራሽ ከቀኑ 6:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት የሚቆይ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም በኣዳራሹ የፀሎትና የዝማሬ መርሃ-ግብር እየተካሄደ ነው፡፡

በመቀጠልም የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ህይወት የሚዘክሩ የተለያዩ ንግግሮች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጀርመናዊቷ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሪጂና አበልክ፣ ልጃቸው አቶ ኢብሳ ነጋሳ እና ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከሚጠበቁት ተናጋሪዎች መካከል ናቸው፡፡

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችም በቦታው በመገኘት አስክሬኑን በክብር እንደሚሰናበቱ ይጠበቃል፡፡

ከቀኑ 8:00 ሰዓት ላይ አስከሬኑ ከሚሌኒየም አዳራሽ ተነስቶ ወደ ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር የሚሸኝ ይሆናል፡፡

ከዚያም ከቀኑ 9:00 ሰዓት ሲሆን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቀብር በብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት የሚፈፀም መሆኑን የወጣው መርሃ-ግብር ያመለክታል።