ዘመናዊ የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለዘመናዊው የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ትምህርት ቤቱ የሚገነባው ፋቲማ ቢን ሙባረክ በተባሉ የዱባይ ዜጋ ድጋፍ ሲሆን ኤፍቢኤም የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ሲያስቀምጡ  እንዳሉት ትምህርት ቤቱ ዐይነስውራን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላል።

ትምህርት ቤቱ ለዐይነ ስውራን ተማሪዎች ምቹ በሆነ ሁኔታ ተገንብቶ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።

በመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ ቀዳማዊት እመቤቷ ከቀዳማዊ ሃይለስላሴ ቀጥሎ የዐይነ ስውራን ጉዳይ ይመለከተኛል በሚል ትምህርት ቤት የሚገነቡ ብቸኛ ሰው ናቸው ብለዋል።

በአገሪቷ ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዐይነ ስውራን ትኩረት ባይሰጣቸውም ቀዳማዊት እመቤቷ ይህን ተግባር መፈጸማቸው የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

ዐይነ ስውራን ካልተማሩ የበለጠ ለችግር ተጋላጭ ከመሆናቸው በላይ በወላጆቻቸው ጭምር መገለል እንደሚደርስባቸውም አንስተዋል።

በሌሎች አገሮች ትላልቅ ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ዐይነ ስውራን መኖራቸውንና በኢትዮጵያ ግን የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ለዐይነ ስውራን እንደማይሰጡ ያነሱት ሎሬት የትነበርሽ፣ ትምህርት ቤቱ ይህን ችግር በመፍታት ዐይነ ስውራን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ኤፍቢኤም የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ11ሺ ሜትር ካሬ ላይ የሚያርፍ ሲሆን 300 ለሚሆኑ ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል።

የሰበታ መርሃእውራን ትምህርት ቤት በአጼ ሃይለስላሴ አገዛዝ ጊዜ የተገነባ የመጀመሪያው የዐይነ ስውራን ትምህርት ቤት ሲሆን ኤፍቢኤም በዘርፉ ሁለተኛው ይሆናል።

(ምንጭ፡- ኢዜአ)