በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ ከተመሰረቱት ክሶች ውስጥ ከ7ኛ እስከ 34ኛ ያሉት በንባብ ቀረቡ

የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ በነበሩት በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ ከተመሰረቱት 46 ክሶች ውስጥ ከ7ኛ እስከ 34ኛ ያሉትን ክሶች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በንባብ አቅርቧል።

በመዝገቡ ክስ ከተመሰረተባቸው 26 ተከሳሾች ውስጥ እስከ 19ኛ ላሉት ተከሳሾች ክሳቸው በንባብ ቀርቦላቸዋል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት ክስ ተመስርቶባቸው ያልተያዙ ተከሳሾች ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት እና ቀሪ ክሶችን ለተከሳሾቹ በንባብ ለማሰማት ለነገ ከሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቃቤ ህግ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኃላፊ የነበሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 ግለሰቦች ላይ በትናንትናው እለት ክስ መመስረቱ የሚታወስ ነው።

በቀድሞው የደህንነት የኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን በአሁኑ ደግሞ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ላይ ሲሰሩ በነበሩ ግለሰቦች ላይም አቃቤ ሀግ 46 ክሶችን መስርቶባቸዋል።

ከተመሰረቱት ክሶች ውስጥም ስድስቱ ክሶች በትናንትናው ዕለት ለተከሳሾቹ በንባብ ቀርበዋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት በዛሬው እለት ቀሪ ክሶችን ለተከሳሾቹ በንባብ ለማሰማት ከሰዓት በኋላ ተሰይሞ ነበር።

ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡት ከ26ቱ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች ናቸው።

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አራቱ ተከሳሾች ማለትም 1ኛ ተከሳሽ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ 9ኛ ተከሳሽ አቶ አፅብሀ ግደይ፣ 11ኛ ተከሳሽ አቶ አሰፋ በላይ እና 12ኛ ተከሳሽ አቶ ሽሻይ ልኡል ለጊዜው ያልተያዙ እና ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ናቸው።

በዛሬው ዕለትም አቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ከመሰረተው 46 ክሶች ውስጥ ከ7ኛ እስከ 34ኛ ያሉትን ክሶች ፍርድ ቤቱ ችሎት ላይ ለተገኙት ተከሳሾች በንባብ አሰምቷል።

ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡት እና ክሳቸው በንባብ ከቀረበላቸው ተከሳሾች ውስጥም አቶ ያሬድ ዘሪሁን እና አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ይገኙበታል።

ፍርድ ቤቱ በንባብ ያቀረባቸው ክሶችም ተከሳሾቹ በተለያዩ የስራ ኃላፊነት በነበሩበት ወቅት በስልጣናቸው እና የስራ ኃላፊነታቸው በማይፈቅደው ህግን በመተላለፍ ከባድ የሙስና ወንጀል በተለያየ መጠን መፈጸማቸውን የሚያስረዱ ናቸው።

የተነበቡት ክሶች ግለሰቦቹ በመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በተለያየ ደረጃ የስራ ኃላፊ ተመድበው ሲሰሩ በህግ አግባብ የተሰጣቸውን ስልጣን መሰረት በማድረግ፥ ተቋሙ የተቋቋመለትን ጥራት ያለውን መረጃ በማቅረብ አስተማማኝ የደህንነት አገልግሎት በመስጠት የሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት የመጠበቅ አላማን ከግብ በሚያደርስ ሁኔታ በስራ ኃላፊነታቸው መወጣት ሲገባቸው ይህን ወደ ጎን በመተው በሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብና በድርጊቱ በመሳተፍ በተለያዩ ግለሰቦች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፅሙ እንደነበር ያስረዳሉ።

በግለሰቦች ላይ ተፈጸሙ ከተባሉ እና በክሶቹ ላይ ከቀረቡት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥም ተከሳሾቹ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ግለሰቦችን በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥራችኋል በማለት በመያዝ እና በተለያዩ የድብቅ እስር ቤቶች እንዲሰቃዩ ማድረግ፣ እንዲገረፉ እና መረጃዎችን በግድ እንዲያወጡ አድርገዋል የሚል ነው።

እንዲሁም በውክልና መረጃ እንዲሰጡ አስገድደዋል፤ በምርመራ ላይ እያሉም ህይወታቸው የጠፋ ግለሰቦች መኖራቸውን እና እስካሁንም እነሱ የያዟቸው ግለሰቦች የደረሱበት ያልታወቀ እና የጠፉም አሉ የሚሉት ይገኙበታል።

በአጠቃላይ ዛሬ የተነበቡት ክሶች ግለሰቦቹ ተበዳዮቹ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈፀምባቸው ያደረጉ በመሆኑ በፈፀሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተከፋይ በመሆን በስልጣን አላግባብ በመገልገል የሚፈፀም ከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የሚያሳዩ ናቸው።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምደብ 1ኛ የወንጀል ችሎት ከ35ኛ እስከ 46ኛ ያሉትን ክሶች ለተከሳሾቹ በንባብ ለማሰማት እና አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ያልተያዙ 4 ተከሳሾች ላይ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ ለነገ ከሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)