ተመድ በየመን የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 3 ሺህ ስደተኞች እንዲለቀቁ ጠየቀ

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት /አይ ኦ ኤም/ በደቡባዊ የመን ኢፍትሃዊ በመሆነ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የታሰሩ 3 ሺህ ስደተኞች እንዲለቀቁ ጠየቀ።

ድርጅቱ እንዳስታወቀው አብዛኛዎቹ በእስር ላይ የሚገኙት ስደተኞች ኢትዮጵያውን ናቸው።

ስደተኞቹ የታሰሩት በኤደንና ላህጅ በተባሉ ከተሞች ሲሆን፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕውቅና የሰጠው መንግስት በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ውስጥ እንደሚገኙም አስታውቋል።

ድርጅቱ 2 ሺህ 500 የሚሆኑት ስደተኞች ኤደን በሚገኝ አንድ ስታዲየም ውስጥ መታሰራቸውን ጠቅሶ፥ ኮሌራ መሰል በሽታዎች እንዳይከሰቱ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል።

እንዲሁም ከየመን መንግስት ጋር ስደተኞቹ በሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አንስቷል።

በተጨማሪም  አይ ኦ ኤም ላህጅ በተባለው ቦታ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የታሰሩ 1 ሺህ 400 የሚደርሱ ስደተኞች ስለመለቀቃቸው ሪፖርት ደርሶታል።

ሆኖም 14 ስደተኞች በውሃ ወለድ በሽታዎች አማካኝነት ህይወታቸው ማለፉ ተጠቅሷል።

የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት 237 የሚደርሱ በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያንን ለመመለስ እየተዘጋጀ ስለመሆኑም ነው ያስታወቀው። (ምንጭ ፡- ኤፍ.ቢ.ሲ)