ኢጋድ እና ኢንተርፖል በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚስችል ምክክር አካሄዱ

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ ኢጋድ/ ከአለማቀፉ ኢንተርፖል ጋር በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚስችል ምክክር አካሂደዋል፡፡

ኢትዮጵያ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ዋነኛ የደህንነት ስጋት አድርጋ ማስቀመጧ የሚታወቅ ሲሆን÷ ኢጋድ እና ኢንተርፖል በቅንጅት መስራታቸው ተጽዕኖውን በመቀነስ ረገድ ኢትዮጵያ የበኩሏን እንድትወጣ ያግዛል ተብሏል፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለታዳጊ ሀገራት ዜጎች  ዋነኛ የፍልሰት ምክንያት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

ከዚህም አልፎ የህገ ወጥ ስደት መዘዝ ለደህንት ስጋት፤ለሽብርተኝነት እና ለሳይበር ጥቃት ሰፊ በር እንደሚከፍት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ያላት ጂኦ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጽዕኖ ስጋት ከደቀነባት ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ኢጋድ ከኢንተርፖል ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል ሀገራቱ ድንበር ተሻጋሪ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጽኖን ለመከላከል በትኩረት እየሰሩ ናቸው፡፡

በኢጋድ የጸጥታና ደህንነት ዋና ዳይሬክትር የሆኑት ኮማንደር አበበ ሙሉነህ እንደሚሉትም እየተራቀቀ በመጣው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ኢንተርፖል በትብብር መስራቱ ኢትዮጵያ ለደህነነት ስጋት ብላ ያስቀመጠችውን ነጥብ እንደሚቀርፍ ተናግረዋል፡፡

በኢንተርፖል ጽ/ቤት የተደራጁና አዳዲስ ወንጀሎች ዳይሬክተር ፖል ስታንድፊልድ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ስልቱን እያሰፋና እየረቀቀ መምጣቱን በማንሳት ተቋማዊና ቅንጅታዊ አሰራር የግድ አንደሚል አመላክተዋል፡፡

በጎርጎሮሳውያኑ 2018/19 150 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለት ለዝውውር መዋሉ በምክክር መደረኩ የተጠቀሰ ሲሆን የሀገራትን ምጣኔ ሀብት በማቆርቆዝ፤ዜጎችን ለሽብርተኛ ቡድኖች ሰለባ ማድረግ እና ከፍ ሲልም የሰውነት አካል ንግድ ሲዳርግ እንደሚስተዋል በመድረኩ ተንስቷል፡፡