ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግሎባል አሊያንስ ለተፈናቀሉ ወገኖች ላበረከተው በጎ ተግባር ምስጋና አቀረበ

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አሊያንስ) ለተፈናቀሉ ወገኖች ላበረከተው በጎ ተግባር ምስጋና አቀረበ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ሊቀ-መንበር አቶ ታማኝ በየነ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ግሎባል አሊያንስ የኢትዮጵያውያን መብት እንዲከበርና ችግር ሲደርስባቸውም ከጎናቸው በመሆን እያደረገ ላለው በጎ ተግባር አቶ ገዱ አመስግነዋል፡፡

ተቋሙ በቅርቡ በጌዲዮ ለተፈናቀሉ ዜጎች ላደረገው ድጋፍና ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ላሳየው አጋርነትም ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ታማኝ በየነ በበኩላቸው ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲቀጥል እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በጎ ፈቃደኛ የዳያስፖራ አባላትን በማሰባሰብ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሙያቸው የድጋፍና የስልጠና እገዛ እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የአሊያንሱን እንቅስቃሴ በማስፋት በተቋማት የአቅም ግንባታና በዴሞክራሲ ማጎልበት ስራዎች ለመሳተፍ መታቀዱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በያዝነው ሳምንት ዓለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት የጌዲኦ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን 31 ሚሊየን 400 ሺህ 700 ብር በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡