ምሁራንን በማሳተፍ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይሰራል – የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እጩ ሃኪሞች ያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስና ችግሩን ለመቅረፍ በዘርፉ ልምድ ያካበቱ እና በሙያው እውቀት ያላቸው ምሁራንን በማሳተፍ እንደሚሰራ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገልጸ፡፡

ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እጩ ሃኪሞች ያነሷቸውን ጥያቁዎች አስመልክቶ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ከወጪ መጋራት ጋር በተያያዘ ክፍያቸው በአገልግሎት እንዲተካ የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቶ እንደነበረ አስታውሰው፣ አሰራሩ በመስተካከል ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  

እጩ ሃኪሞቹ ከመምህራኖቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራ ነው ሚኒስትር ዲኤታው የገለጹት፡፡

እጩ ሃኪሞቹ በአንዳንድ ተቋማት የትምህርት ማቆም አድማ ሲያደርጉ እንደነበረና ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትምህርት በማይመለሱ የህክምና ተማሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡