ሕገወጥ የመሬት ወረራ ላይ አስተዳደሩ እርምጃ እንደሚወስድ ገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ በተደራጀ መልኩ እየተደረገ ያለው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ላይ የከተማ አስተዳደሩ እርምጃ እንደሚወስድ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በከተማው  እየተበራከቱ ያሉ የመሬት ወረራ እና በህገ-ወጥ ቤቶች ዙርያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በጤናማ ከተማ ውስጥ መኖር የሁሉም ነዋሪ ህጋዊ መብቱ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ የህግ አግባብነት የሌላቸው የህገ-ወጥ ቤቶች ግንባታ እና የመሬት ወረራ በከፍተኛ ሁኔታ መበራከቱን ገልፀዋል ፡፡

በተለይም በቦሌ፣ የካ፣ ኮልፌ፣ ነፋስ ስልክ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በተደራጀ መልኩ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

ባለሃብቶች ፣ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ፣ ደላሎች እና የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ጭምር በሚሳተፉበት ህገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ እና የመሬት ወረራ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከማፍረስ በተጨማሪ እነዚሁ አካላት በህግ እንዲጠይቁ ይደረጋል ብለዋል። 
ውስን የሆነዉን የህዝብ ሃብት ከህገወጦች ለመከላከል አስተዳደሩ የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ሃላፊነቱን እንደሚወጣም ተናግረዋል ፡፡

ከመሬት ወረራው በተጨማሪም የከተማውን ነዋሪ ሰላም የሚያውክ ማንኛውም ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላትን የከተማ አስተዳደሩ እንደማይታገስ እና እርምጃ እንደሚወስድም ተናግረዋል፡፡

(የከንቲባ ጽ/ቤት)