የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ተፈናቅለው ለነበሩ ዜጎች ድጋፍ አደረገ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ በክልሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በቅርቡ ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለተመለሱ ዜጎች ለዘር እና ማዳበሪያ ግዢ የሚውል ከ627 ሚልዮን ብር በላይ በድጋፍ እና በብድር መልክ እንዲሰጥ ወሰነ፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ ስምንት ዞኖች በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ የተደረጉ ዜጎች በመደበኛ የግብርና ስራቸው ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ እና ከእለታዊ ድጋፍ ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ በማሰብ ለዘር እና ማዳበሪ ግዢ ወጪ እንዲደረግ ነው ውሳኔውን ያስተላለፈው፡፡

ከተወሰነው ብር ውስጥ 169 ሚልየን 825 ሺህ 541 ብር ለዘር ግዢ በድጋፍ እንዲሰጥ የተወሰነ ሲሆን ቀሪው ብር ደግሞ በብድር መልክ እንዲቀርብ ምክር ቤቱ መወሰኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድማሱ ዳምጠው ለዋልታ ገልፀዋል፡፡

ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ቦረና፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቀያቸው የተመለሱ  አርሶ አደሮች የድጋፉ እና የብድሩ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽንና ግብርና ቢሮ አፈፃፀሙን እንዲከታተሉ እና ለአርሶ አደሮቹ በጊዜ ግብአት እንዲደርስ የክልሉ ካቢኔ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡