ጠ/ሚ ዐቢይ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት መሪዎች ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ከ400 ያህል የወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት መሪዎች ጋር ተወያዩ።

ውይይቱ በተለያዩ የወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት መሪዎች መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ይህም በአሁኑ ወቅት በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል እየታየ ያለውን የመከፋፈል አዝማሚያ ለማስቀረት ያስችላል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ።

ሃይማኖቶች በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የሃይማኖት ተቋማት ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እርስ በርስ በመናበብ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም የሃይማኖት ተቋማት ያሏቸውን ልዩነቶች በማክበር የሚመሳሰሉባቸውን ጉዳዮች ለማጉላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።

የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችም ለተከታዮቻቸው ዓርአያ ሊሆን የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባቸው ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ችግር ለመቅረፍም እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ፈቃድ በሚያወጡበት እና በሚያሳድሱበት ጊዜ ያሉ ችግሮችን፣ አንዳንድ የመንግስት ተቋማት በአብያተ ክርስቲያናት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የመግባት ሁኔታንና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተዋል።