አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 6ሺ 857 ተማሪዎችን አስመረቀ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸዉን 6ሺ 857 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ፡፡

በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ጋርዳ እንደተናገሩት 1979 ዓ.ም 45 ተማሪዎችን በመቀበል የትምህርት ስልጠና የጀመረዉ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የዛሬዎቹን ተመራቂዎች ጨምሮ እስካሁን ድረስ 54 ሺ 632 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ ባሉት ስድስት ካምፓሶቹ በትምህርት ዘመኑ በተለያዩ የትምህርት መርሀ-ግብሮች 35ሺ 942 ተማሪዎችን እያስተማረ ነዉ ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለዉም እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲዉ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ካሉት 1ሺህ 009 መምህራን መካከል 620 የሚሆኑትን የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት በሀገር ዉስጥና በዉጭ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት እያስተማረ ነዉ፡፡

በ2011 ዓ.ም 53 ሚሊዮን ብር በመመደብ ብዙ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ ከነዚህ ዉስጥም 60 የሚሆኑት በዓለም አቀፍ ሕትመት መብቃታቸውን ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ የቦርድ ሰብሳቢና የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ መንግስት ለትምህርት በተለይም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ በጀት መድቦ ዜጎችን እያፈራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተስፋና ስጋት  መንገድ ላይ እንደመሆኗ መጠን ተመራቂ ተማሪች በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙ ሀሰተኛና የዘረኝነት ሀሜትን በመዋጋት በሀገር ግንባታ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዶክተር ይናገር ጠይቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ በግጭት አፈታትና ሰላም ማስጠበቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የጋሞ አባቶችም እዉቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡