በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው የእውቀት ሽግግር እያደረጉ መሆናቸውን ገለጹ

በኬንያ በተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በመድረክ ተሰባስበው ወደ ሀገር ቤት የእውቀት ሽግግር እያደረጉ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

በኬንያ ናይሮቢ 56 አባላትን አቅፎ ከተመሰረተ አንድ ዓመት የተሻገረው የእነዚህ ኢትዮጵያውን ምሁራን መድረክ ለሀገራቸው የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በተሰማሩበት የሙያ የዕዉቀት ሽግግር ማድረግ መጀመራቸውን አሳውቀዋል፡፡

ኑሮአቸውን በውጪ አገራት ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ በተለያዩ የሙያ መስክ የተሰማሩ በመሆኑ ያካበቱትን እውቀቶች ለሀገር ቤት እንዲያሸጋግሩም ምሁራኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እየተስተዋለ የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ኬንያን በጎበኙበት ወቅት ባቀረቡት ጥሪ መመስረቱ የሚነገርለት ይህ የምሁራን መድረክ፣ በኬንያ የሚገኙና በተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን በማሰባሰብ መድረክ ፈጥረው ሀገራቸውን በሃሳብ፣ በፖሊሲ ቀረጻ እና በተለያዩ መስኮች ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን አባላቱ ለዋልታ ቴሌቪዥን ገልጸዋል፡፡

ምሁራኑ ከሙያ መስካቸው ጋር ተቀራራቢነት ካላቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀራረብ የልምድ ማካፈል ተግባር መከወን መጀመራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም የትውልድ ግንባታ ላይ አተኩረው ይሰራሉ፤ ያካበቱትን ሙያዊ እውቀታቸውን ያሸጋግራሉ፡፡

ውጭ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በፖለቲካ እና በተለያዩ አመለካከቶች ተለያይተው ከመቃረን ይልቅ ማበርከት የሚችሉ የልማት ድጋፍ ላይ ቢያተኩሩ ሲሉም ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡

መድረኩ ከፖለቲካ እና ሃይማኖት ልዩነት ነጻ ሆኖ ለመስራት የሚያስችል የሥራ መመሪያ ማስቀመጡን አሳውቋል፡፡

የመድረኩ ዋነኛ ውጥንም ተምሳሌት ያለውን ተግባር በመከወን ለትውልድ መልእክት ማስተላለፍ መሆኑን ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡