የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 4 ሺህ 44 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ አስመረቀ

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በዛሬው ዕለት 4 ሺህ 44 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ አስመረቀ፡፡

ዩኒቨርስቲው ዘንድሮ ለ11ኛ ዙር ያስመረቀ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት ሰዎች የክቡር የዶክተሬት ዲግሪ ሰጥቷል፡፡ የክቡር ዶክተሬት ያገኙት ሰዎችም ዘብዲዮስ ጨማ እና ደጃዝማች ወልደሰማያት ገብረወልድ ሲሆኑ፤ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በባህል ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው ተብሏል፡፡

በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርስቲው ቦርድ አስተዳደር ሰብሳቢ ዶክተር ቶላ ባርሶ ለተማሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ቦርዱ ለተቋሙ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ከዩኒቨርስቲው ጎን እንደሚቆምም አስታውቀዋል፡፡

በዕለቱ የክቡር እንግዳ የሆኑት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ዩኒቨርስቲው በክህሎትና በዕውቀት የዳበረ የሰው ኃይል እያፈራ መሆኑን ገልጸው፣ ተማሪዎች የዘረኝነትና የጎጠኝነትን መንፈስ በመተው ለኢትዮጵያ ሰላም ዘብ ሊቆሙ ይገባል ሲሉ ለተመራቂዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዩኒቨርስቲ ቆይታ ያካበቱትን ዕውቀትና ልምድ ለወደፊቱ የችግር መፍቻ ቁልፍ አድርገው እንዲገነዘቡም ጠቁመዋል፡፡

በሀገሪቱ ያለውን የስራ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀምም ለኢትዮጵያ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፈሰር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው እስካሁን የዘንድሮ ተመራቂዎችን ጨምሮ ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቀው ለሀገሪቱ የሰው ኃብት ልማት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ 2011 የትምህርት ዘመን 54 የማህበረሰብ ዓቀፍ አገልግሎቶች፣ 99 የምርምር ስራዎች እና አምስት የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት ማከናወኑንም ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በቀጣይ ሳምንት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅም አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በ11ኛ ዙር በተለያየ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 64 ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎች የፖለቲካና የግለሰቦች አጀንዳ ማራመጃ ስፍራዎች ሳይሆኑ ወጣቶች በእውቀትና በክህሎት ሰልጥነው ለሀገር ልማት አስተዋጥኦ እንዲያበረክቱ የሚቀረፁበት እንደሆነም በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡