ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ከማላላ ዩሱፍዛይ ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሠላም ዘርፍ ኖቤል ተሸላሚና የመንግስታቱ ደርጅት የሠላም መልዕክተኛ ማላላ ዩሱፍዛይ ጋር ተወያዩ፡፡

ፕሬዚዳንቷ በዚህ ውይይታቸው ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተሻለ ሁኔታ መማር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ መምክራቸው ተገልጿል፡፡

መንግስት ያለውን የትምህርት ፖሊሲ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልክ ለማሻሻል የትምህርት ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፣ በዚህ ዙሪያ ማገዝ ለሚፈልግ ማንኛውም አካል አስፈላጊ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይም በሴት ተማሪዎች ላይ የሚታየውን የትምህርት ማቋረጥ ለመቀነስ በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርና አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የሠላም ዘርፍ ኖቤል ተሸላሚና የተባበሩት መንግስትታት ደርጅት የሠላም መልዕክተኛ ማላላ ዩሱፍዛይ በስሟ የሚጠራው ፋውንዴሽን ለሴት ተማሪዎች ትኩረት ሠጥቶ በዓለም ደረጃ እየተንቀሳቀሰ የተለያዩ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግራለች፡፡

በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ተግባራትን በማከናወን ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ማገዝ እንደምትፈልግ አስታውቃለች፡፡

ማላላ ፋውንዴሽን በአውሮፓዊያኑ 2013 በእንግሊዝና በአሜሪካ መሰረቱን በማድረግ የተመሰረተ ሲሆን፣ እንደ ሊባኖስ፣ ቱርክ፣ ኬኒያ፣ ናይጀሪያና ሴራሊዮን በመሳሰሉት ሀገራት በሴቶች ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ከፕሬዚዳት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡