ለሐጂ ተጓዦች ሽኝት ተደረገላቸው

የ2011 ዓ.ም የሐጂ ተጓዦች በኢትዮጵያ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር እና የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በተገኙበት ሽኝት ተደረገላቸው፡፡

በሽኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር እንድሪስ የሐጂ ጉዞ የተሳካ እንዲሆን ትብብር ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የሳዑዲ መንግስት የፈቀደው የተጓዦች ቁጥር 10 ሺህ እንደሆነና እስከሁን ከ18 ሺህ በላይ ተጓዦች መመዝገባቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ የተመዘገበው የተጓዥ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ኮታ ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር ሳሚ አብዱላ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ምንም ዓይነት ችግር እንዳያጋጥማቸው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ተጨማሪ የተጠየቀውን ኮታ ለመፍቀድም ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራአስፈጻሚ ተወካይ አቶ መስፍን ጣሰው ለሐጂ ተጓዦች 19 በረራዎች መታቀዳቸውን ተናግረው፣ እንደተጓዡ ቁጥር ሊጨመር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ተጓዦቹ የበረራ ሰዓት እስኪደርስ እንዳይጉላሉ የእንግዳ ማረፊያ ማዘጋጀታቸውንም አስታውቋል፡፡