ጋዜጠኛ መስፍን ሽፈራው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ጋዜጠኛ መስፍን ሽፈራው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ጋዜጠኛ መስፍን ሽፈራው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ለረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነትና በሌሎችም የስራ ዘርፎች በባለሙያነትና በሃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

ጋዜጠኛ መስፍን ከአባታቸው ከአቶ ሺፈራው ኃይሉ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ውቤ ገሰሰ በ1955 ዓ.ም በቀድሞ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ሀብሮ አውራጃ ቁኒ ወረዳ በዴሳ ቀበሌ ተወለዱ።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በበዴሳ አንደኛ ደረጃ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጨርጨር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

ጋዜጠኛ መስፍን ሽፈራው የከፍተኛ ትምህታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጆኦግራፊ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

በስራ ዓለምም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከጠቀጠሩበት ከጥቅምት 10/1980 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 10/1998ዓ.ም ድረስ በጋዜጠኝነት ሙያ በአዘጋጅነት፣ የሽፍት እንዲሁም የክልል ዜና ማስተባባሪያ ዴስክ ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሲቪል ሰርቪስ ኃላፊ በመሆን፤ ከዚያም በፊት  በማዕከላዊ ፕላን ጽህፈት ቤት ማገልገላቸውን የግል ማህደራቸው ያስረዳል።

መስፍን ሺፈራው ከየካቲት 10/1998 ዓ.ም በዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት የመረጃና ጥናት ትንተና ዋና ክፍል ሃላፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፤ ከመጋቢት 1/2004 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በሃላፊነት ማገልገላቸውንም የግል ማህደራቸው ያስረዳል።

ጋዜጠኛ መስፍን ሺፈራው በባለሙያነትና በስራ ኃላፊነት ባገለገለባቸው ዓመታት ምስጉን ከስራ ባልደረቦቹም ተግባቢ፣ ቅንና መልካም ግንኙነት እንደነበራቸው ባልደረቦቻቸው ይመሰክራሉ።

መስፍን ሺፈራው ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው፤ በ56 ዓመታቸው ሐምሌ 8/2011ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የጋዜጠኛ መስፍን ሽፈራው የቀብር ስነ-ስርዓት ዛሬ ሐምሌ 9/2011 ዓ.ም በእንጦጦ ኪዳነ ምህረት  ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና የስራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል።

ጋዜጠኛ መስፍን ሽፈራው ባለትዳር፤ የአንድ ወንድ እና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።