የሚረጋ ዘይት አዘውትረው በሚመገቡ ሰዎች ላይ የስትሮክ ህመም እንደሚያስከትል ተገለጸ

የሚረጋ ዘይት ከፍተኛ የስብ ክምችት በመያዙ አዘውትረው በሚመገቡ ሰዎች ላይ የስትሮክ ህመም ያመጣል – የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትኢትዮጵያ በየአመቱ 450 ሺህ ቶን የሚረጋ ዘይት በከፍተኛ ድጎማ ከውጭ እንደምታስገባ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዚሁ ምርት ላይ ለአራት ወራት ጥናት ማድረጉን እና ምርቱም ከፍተኛ የስብ ክምችት በመያዙ አዘውትረው በሚመገቡ ሰዎች ላይ የስትሮክ ህመም እንደሚያመጣም ገልጿል፡፡

80 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያዊያን የዚሁ ምርት ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም ኢኒስቲትዩቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ምርቱን ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት ለተጠቃሚው የሚያደርሰው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በየወሩ 48 ሚሊዮን ሊትር ለምግብነት እንደሚውል ጠቅሶ ከዚህም ውስጥ 40 ሚሊዮን ሊትሩ ከፍተኛ የስብ ክምችት የያዘው ዘይት ነው ብሏል፡፡

ምርት በጊዜ ሂደት በተጠቃሚው ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ እየታወቀ ስለምን ለህብረተሰቡ ሊቀርብ ቻለ ለሚለው ጥያቄ “ለበሽታ የመጋለጥን ጉዳይ ለጤና ባለሙያዎች እንተወው፤ የኛ ስራ የዘይት አቅርቦቱ ተደራሽ እንዲሆን ማስቻል ነው” ሲሉ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ተናግረዋል፡፡

ምርቱ ወደ ሃገር እንዲገባ ጥራቱን የሚፈትሸው የኢትዮጵያ ምግብ፣ መድሃኒትና ፋርማሲዩቲካል ቁጥጥር ባለስልጣን እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ምርቱን እንድታስገቡ ፈቃድ ተሰጥቷችኋል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም የማይመለከታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምግብ፣ መድሃኒትና ፋርማሲዩቲካል ቁጥጥር ባለስልጣን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡