ኢትዮጵያ እና ዩኒሴፍ የ1.4 ቢሊየን ብር ስምምነት ተፈራረሙ

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና ከመንግስታቱ ድርጅት የስነ ህዝብ ፈንድ ጋር የ49 ሚሊየን ዶላር (1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር) ስምምነት ተፈራረመች።

ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊየን ዶላሩ የመንግስታቱ ድርጅት የስነ ህዝብ ፈንድ ድርሻ ነው።

ስምምነቱን የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ኤዴሌ ኮድር ተፈራርመውታል።

ስምምነቱ ዩኒሴፍ በ2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለሚያከናውናቸው ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል ነው ተብሏል።

በስምምነቱ መሰረት በህጻናት ጤና፣ ንጽህና፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ ትምህርትና የህጻናት መብትን ጨምሮ የተለያዩ 16 ፕሮግራሞች ይተገበራሉ።

ፕሮግራሞቹ በኢትዮጵያ የሚገኙ ህጻናትን ጤናማ አስተዳደግ ለማሻሻልና በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ጥቃት ለመከላከልና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚያግዙ ናቸው።

በቀጣዩ አመት የሚተገበረው ይህ ፕሮግራም ዩኒሴፍ ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2020 በኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት የልማት አጋርነት ስር የሚተገብረው የመጨረሻው ፕሮግራም ይሆናልም ተብሏል።

ቀጣዩ የዩኒሴፍ ፕሮግራም የ2012 በጀት አመት ከተጠናቀቀ በኋላ ለአምስት አመታት በቀጣይነት እንደሚተገበር ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።