የአፍሪካ ቀን በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከበረ

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አብዱልአዚዝ አህመድ ኢትዮጵያ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት እንዲመሰረት የተጫወተችው ሚና በአፍሪካውያን መካከል መተባበርንና የዓላማ አንድነትን እንዲኖር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ሥርዓት እንዲወጡ ያደረገችው ተጋድሎና ከፓን አፍሪካዊ ንቅናቄ እና እሳቤ ጋር ጠንካራ ቁርኝት እንዳለውም አንስተዋል፡፡

በቅርቡ በአፍሪካ መሪዎች ደረጃ የተፈረመው ነፃ የአፍሪካ የንግድ ቀጠና ስምምነት የአፍሪካ ህብረት በኢኮኖሚ መስክ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ እርምጃ የተራመደ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም አምባሳደር አብዱልአዚዝ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ቀን የሚከበረው ይህንን የአፍሪካውያንን ህብረት እና አንድነት ዓላማ ግብ ለማድረስ ታስቦ እንደሆነም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በአፍሪካ ቀን ክብረ በዓል ተሳታፊ የነበሩ አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ አገራት ዲፕሎማቶችና የኮሚኒቲ ተወካዮች እንዲሁም ተጋባዥ ባለሃብቶች የተዘጋጀውን የባህላዊ ምግብ ዝግጅትና የኤግዚቢሽን ሥፍራ ጎብኝተዋል።

በሪያድ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎችም የአገራቸውን ውበትና ጥበባት፣ ሥነ-ምግብ ውጤቶች፣ አልባሳትና እደ ጥበብ ውጤቶች እንዲሁም የቱሪዝም ሃብት መዳረሻ ሥፍራዎችን ማስተዋወቅ መቻላቸውን በሪያድ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተላከልን መረጃ ያሳያል፡፡