ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አይነስውራን ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብለው አነጋገሩ

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በትምህርት ቆይታቸው በጸሃይ ዘውዴ መታሰቢያ ስኮላርሽፕ ፕሮግራም ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩ እና በዚህ አመት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሴት አይነስውራን ተማሪዎችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ተመራቂዎቹ ከተለያዩ የትምህርት መስኮች የተውጣጡ ሲሆን፣ ትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅትም በስኮላርሽፕ ፕሮግራሙ በየሶስት ወሩ 900 ብር ድጋፍ ሲደረግላቸው ከመቆየቱም በላይ የኮምፒውተር ስልጠናና ለትምህርታቸው አገልግሎት የሚውሉ መረጃዎችን ለመቅዳት የሚውሉ ድጅታል መሳሪያዎች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብለው ያነጋገሩት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ተማሪዎችን በአስቸጋሪና ውጣ ውረድ በሞላበት ሁኔታ ውስጥ ላስመዘገባችሁት ውጤታማነት "እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል፡፡

"እናንተ ለሌሎች ምሳሌ ናችሁ፤ የማይቻል ነገር እንደሌለ አሳይታችኋል፤ መጪው ብሩህ ጊዜ የእናንተ ስለሆነ በአሁኑ አይነት ቁርጠኝነታችሁ ጉዟችሁን ቀጥሉ" ሲሉም አበረታቷቸዋል፡፡

ተመራቂ ሴት አይነ ስውራን በበኩላቸው፣ ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉና የህይወት ጉዟቸው ትክክለኛውን አቅጣጫ እንዲይዝ ለተደረገላቸው ድጋፍና ማበረታቻ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

"ይህ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ መዳረሻችን ከዚህ መልካም ሁኔታ የተለየ በሆነ ነበር" ብለዋል፡፡

የጸሃይ ዘውዴ መታሰቢያ ስኮላርሽፕ ፕሮግራም የዛሬ 24 አመት በኮሞሮስ ደሴቶች ላይ በተከሰከሰው የኢትዮያ አየር መንገድ ላይ ህይወቷ ያለፈውና የክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ታናሽ እህት በሆነችው ሊድ ሆስተስ ጸሃይ ዘውዴ መታሰቢያነት የዛሬ ዘጠኝ አመት የተመሰረተ ድርጅት ነው፡፡ መረጃው የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ነው፡፡