በዞኑ ሃገረስብከት በሚገኙ 2ሺ ቤተክርስቲያናት 3ሚሊዬን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

በደቡብ ጎንደር ዞን ሃገረስብከት ሠራተኞ የአራቱ ጉባኤ መምህራንና ተማሪዎች በደብረታቦር ከተማ ሐየር አካዳሚ ቅጥር ግቢ ዛሬ ችግኞችን ተከሉ።

የደቡብ ጎንደር ዞን ሐገረ-ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ፀሐይ ፀዳሉ ታደሰ እንዳሉት፤ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትልልቅ መገለጫዎች መካከል የደን ልማትና ያለማችዉን ጠብቆ ደንን ለትዉልድ ማስረከብ ነዉ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ችግኞችን ለመትከል በተሰጠው ትኩረት መሰረት በዞኑ በሚገኙ 2ሽህ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም ድረስ 3 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል ብለዋል ፡፡

በእያንዳንዱ ቤተክርስቲያን የሚተከሉት ችግኞች ተጠብቀዉና እንክብካሜ ተደርጎላቸዉ ለፍሬ እንዲበቁም ክትትል ይደገራልም ብለዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ሃገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የኦርቶዶክስ ቤተክስቲያን ታሪክ ዛፍና ደን ልማት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቆመዉ፤ ቤተክርስቲያኗ እስከ አሁንም ድረስ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩና በማንኛዉም ቦታ የማይገኙ የዛፍ ዝርያዎችን ጠብቃ የምትገኝ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመትም በመንግሥት በኩል በአገር ደረጃ በተሰጠዉ ትልቅ ትኩረት መሰረት ቤተክርስቲኗ የድርሻዋን ለመወጣት እየሠራች ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ለተከላቸዉ ችግኞችም ትኩረት ሰጥቶ መንከባከብ እንዳለበት አባታዊ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት