የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 9 ሺህ 750 ተማሪዎችን አስመረቀ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 9 ሺህ 750 ተማሪዎችን አስመረቀ

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይየባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ  እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው 9ሺህ 750 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፤ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ በተለያዩ መርሃ ግብሮች አስመርቋል።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንድ እንደገለጹት፤ ከተመራቂዎች መካከል 6 ሺህ 520 ያህሉ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 3 ሺህ 167 በሁለተኛ ዲግሪና 63 በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛ በሆነበት በማሪታይም አካዳሚ ጭምር በርካቶችን እያስመረቀ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ፍሬው፤ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት ተወዳዳሪነቱ በየጊዜው እያደገ መምጣቱን አብራርተዋል።

በሕግ ትምህርት ቤት በሃገር አቀፍ ደረጃ 1ኛ እና 3ኛ ደረጃ የያዙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውንም በአብነት አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎችን ለሕይወት ዘመን የሚበጁ ዕውቀቶችን እንዳስታጠቃቸው በመግለጽ፤ በምክንያታዊነት የሚያምኑ ሃገር የሚገነቡ ዜጎች እንዲሆኑም ተመራቂዎቹን አሳስበዋል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ336 ፕሮግራሞች እያስተማረ ይገኛል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ስርዓት ለሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጦፋ ሙህመድ ዑመር የክብር ሜዳልያ ሸልሟል፡፡

የክብር ሜዳልያውን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌውና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ አበርክተውላቸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ መስኮች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡት ዶ/ር ሰገነት ቀለሙ፤ ፕሮፌሰር ሀንስ ማትሰን እና ማርክ ጌልፋንድ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።

ዶክተር ሰገነት ቀለሙ በልዩ መሪነትና ተመራማሪነት ዘርፍ የተመረጡ ሲሆን ናይሮቢ የሚገኘው ዓለማቀፉ የነፍሳት ግብረ አካል እና ሥነ-ምኅዳር የመጀመሪያዋ ሴት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡

ከ25 ዓመታት በላይ በሰሜን አሜሪካና በላቲን አሜሪካ በርካታ ምርምሮችን ሠርተዋል፡፡

በዓለማቀፍ ደረጃ ዕፅዋትን በሚያጠፉ በሽታዎች ላይ ሳይንሳዊ ምርምር በማድረግ ቀዳሚ ሴት ተመራማሪ በመሆናቸውም በርካታ ሽልማቶችን አሸንፈዋል፡፡

ስዊድናዊው ፕሮፌሰር ሃንስ ማትሰን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና በምሥራቅ አፍሪካ የመሬት አስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

አሜሪካዊው ማርክ ጌልፋንድ በበኩላቸው: በኢትዮጵያና በሌሎች ታዳጊ ሀገራት የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምሕንድስና እና የሒሳብ ትምህርቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው ድጋፍ ያደረጉ ምሁር ናቸው፡፡

በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በአዲስ አበባና በሌሎችም 12 ዩኒቨርሲቲዎችና አካባቢዎች የስቲም ማዕከላት እንዲከፈቱ ድጋፍ አድርገዋል።