ባለስልጣኑ ከ1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከልና ለመንከባከብ መዘጋጀቱን አስታወቀ

ባለስልጣኑ ከ1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከልና ለመንከባከብ መዘጋጀቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች ከ1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከልና ለመንከባከብ ዝግጅት ማድረጉን እስታወቀ።

የባለስልጣኑ ሰራተኞችና አመራሮች ዛሬ ባደረጉት የችግኝ ተከላ ወቅት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኘ ”ልጅ እያሉ ችግኝ እተክል ነበር በተለይ እኔ ያደኩበት አካባቢ ያኔ የደን ሽፋኑ ጥሩ ነበር እያደኩ ስመጣና ወደ ትምህርቱ ሳተኩር ችግኝ መትከሉን እየተውኩት መጥቼ ነበር አሁን ግን ያጠፋሁትን ጊዜ ማካካስ እፈልጋለሁ” ይላሉ ።

ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን ከአረንጓዴ ልማት ውጭ ማሰብ የማይቻል ነው ስለሆነም ትላንት ያራቆትነውን መሬት ለመሸፈን እየታገልን እንገኛለን ይላሉ።

ኢንጅነሩ በትዝታ ወደ ኋላ ተመልሰው በቁጭት ኢትዮጵያ ከአመታት በፊት ለምለሚቱ ኢትዮጵያ ትባል ነበር ዛሬ እኛ ላራቆትነው መሬት እዳ አለብን ይህን ደግሞ እንደዚህ በየክረምቱ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ መክፈል ይኖርብናል ሲሉም አከለዋል።

ሌላኛዋ ችግኝ በመትከል ላይ ያገኘናት የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ነፍሰጡር ስትሆን እንዴት በዚህ አስቸጋሪ የአየር ንብረት ልትመጣ እንደቻለች ጠይቀናት ይህ የኔ እና የልጄ አሻራ ነው ለነገው መልካም ዘመን የማበረክተው ስጦታ በማለት መልስ ሰጠችን።

ችግኝ መትከልን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እንደ በጎ ፈቃድ የሚያከናውነው ሳይሆን ግዴታውም ጭምር ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ለመንገድ ስራ የምንመነጥረውን ደን መተካት አለብን ለዚህም በተቋማችን ከሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞችም ችግኝን መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት ብለዋል፡፡