የአማራ ክልል የ2012 ዓ.ም በጀት 47 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ሆኖ ጸደቀ

የአማራ ክልል የ2012 ዓ.ም በጀት 47 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ሆኖ ጸደቀ

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጥላሁን መሐሪ የበጀት ዓመቱን የማስፈጸሚያ በጀት ለክልሉ ምክር ቤት አቅርበዋል፤ ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡

ዕቅዱ ካለፈው በጀት ዓመት በብር 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱን ቢሮ ኃላፊው ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

በጀቱ የተጀመሩ እና በአዲስ የሚጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ያልተሳኩ ዕቅዶችንም ለማሳካት፣ ለድህነት ተኮር ዘርፎች ትኩረት ለመስጠት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራው እና ሌሎችም ዐበይት ተግባራት ማስፈጸሚያነት እንዲሆን ታስቦበት እንደተዘጋጀ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በበጀት አጠቃቀም በኩል ጥንቃቄ በማድረግ ለታለመለት ተግባር ብቻ ማዋል እንደሚገባም ቢሮ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ  አቶ አገኘሁ ተሻገርን የክልሉ የሰላም ግንባታና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሹሟል፡፡

አቶ አገኘሁ ላለፉት 20 ዓመታት በክልሉ በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች እንደሰሩ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

አቶ አገኘሁ ከሰላምና ጸጥታ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ልምድ ያላቸው በመሆኑ፤ ለወቅቱ የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ መረጋጋት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ምክር ቤቱ ሹመቱን በሙሉ ድምጽ ነው ያጸደቀው። የአማራ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገበው።