ችግኞች መጽደቃቸው ተረጋግጦ ለተከሏቸው አካላት የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ

በኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የሚካሄድበትን ‹‹የአረንጓዴ አሻራ›› ቀን በተመለከተ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መግለጫ ሰጥቷል።

ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም በአማራ ክልል በአንድ ቀን 100 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታሰቡን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ወንዴ ገልጸዋል።

በተያዘው ክረምት በአማራ ክልል ከ2 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስታውቀው፤ እስካሁንም 800 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል ብለዋል።

ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 12:00 እስከ ምሽቱ 12:00 በአንድ ጀምበር በአገሪቱ ከሚኖረው 200 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ፤ ከእቅዱ ውስጥ ግማሹን መትከል ደግሞ አማራ ክልል ኃላፊነት ወስዷል ብለዋል።

ዋናው ጉዳይ ችግኝ መትከሉ ሳይሆን መንከባከቡ እንደሆነ የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ፤ ግለሰቦችና ተቋማት ችግኞችን ስለማጽደቃቸው ክትትል እንደሚደረግና ከሁለት ዓመት በኋላ ችግኞቹን በሚገባ ማጽደቁ ተረጋግጦ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የሀሰት ሪፖርትን ለመከላከል፣ ስለተተከሉትና ስለጸደቁት ችግኞች ብዛትም ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል አሠራር እንደተዘጋጀም ሃላፊው ገልጸዋል።

(ምንጭ፡ አብመድ)