የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለአማራ ሕዝብ ክልል ሕዝብ ሠላምና ደኅንነት የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ክልሎች ሠላምና ፀጥታም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ለክልሉ ሕዝብ ሠላምና ደኅንነት ሲባል ከሌሎች ክልሎች ጋር በሠላም ጉዳይ ለመሥራት በራቸው ድረስ ለመሄድ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሠላምና ፀጥታ በቅድሚያ የሚጠቅመው የክልሉን መሆኑን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥የአማራ ክልል ሕዝብ ከክልሉም ውጭ ስለሚኖር የሌሎች ክልሎች ሠላምና ፀጥታ የአማራ ክልልም ጉዳይ በመሆኑ ከክልሎች ጋር አብረን ለመሥራት ተዘጋጅተናል ነው ያሉት፡፡
ወደ ስልጣን የመጣሁበት ወቅት የክልሉ ሕዝብ በታሪኩ አይቶት በማያውቀው መልኩ አሳዛኝ ክስተት የተፈጠረበት ነው፥ ያሉት አቶ ተመስገን ክልሉን ከዚህ ችግር ለማውጣትና የፀጥታ ስጋት የማይፈጠርበት እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉን ሠላምና ፀጥታ ማስጠበቅ የፀጥታ ኃይሉ ብቻ ኃላፊነት አለመሆኑን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ለክልሉ ሕዝብ ሠላም አበክረው ሊሠሩ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የሕዝቡን የሠላምና የፀጥታ ስጋቶች በመለየት መሥራት የሚዲያው ተቀዳሚ ተግባር መሆኑንም ጠቁመዋል ።
ከዚህ ባለፈም ሚዲያዎች የምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴቶችን ሽፋን መስጠት አእንዳለባቸው መጠቆማቸውን አብመድ ዘግቧል፡