የዙና ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ

የዙና ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ጌታሰው በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ300 ሺህ ብር ተቀጡ።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው ዕለት የዙና ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዘሪሁን ጌታሰውን ጉዳይ ተመልክቷል።

አቶ ዘሪሁን ከ109 ግለሰቦች ሲኖትራክ ተሽከርካሪ አስመጣለሁ በማለት በአጠቃላይ ከ73 ሚሊየን ብር በላይ በማጭበርበር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዙና ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ጌታ ሰው ላይ 122 ክሶችን መመስረቱም ይታወሳል።

በዚህም ከ109 ግለሰቦች ከ 2 ሚሊየን 600 ሺህ እስከ 314 ሺህ ብር መኪና አስመጣለው በማለት ባጠቃላይ ከ73 ሚሊየን ብር በላይ ተቀብላለው መሰወራቸው በክሱ ተመላክቶ ነበር።

በክሱ መሰረትም አቃቤ ህግ አለኝ ያለውን የሰነድ ማስረጃ እና የግል ተበዳዮችን ምስክርነት አቅርቦ አሰምቷል።

ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር ያቀረቡ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት 13 ክሶችን ውድቅ በማድረግ ተከሳሹን በ109 ክሶች ጥፋተኛ ብሏል።

በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ የዙና ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ጌታሰው በ14 ዓመት ፅኑ እስራትና በ300 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ መወሰኑን ኤፍቢሲ ዘግቧል።