2ኛው ዓለምአቀፍ የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጉባዔ በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት የስብሰባ ማዕከል እየተካሄደ ነዉ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ጉባዔውን በይፋ በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በማደግ ላይ ላሉ አገራት ድህነትን ለመቀነስና ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ዘርፉ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
የኢትዮጵያን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በመደገፍ ድርሻውን ለተወጡት ድርጅቶች ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብዲዋስ አብዱላሂ በበኩላቸው ጉባዔውን የኢትዮጵያን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ያለበትን ደረጃ ለማሳየት፣ በዘርፉ ያሉ ችግሮችንና ለችግሮቹ መፍቻ የሚሆኑ ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
በመደረኩ የተለያዩ አገራት በተለይም እንደ ማሌዢያ፣ ፊሊፒንስ እና ኢንዶኒዢያ ተሞክረሮ ምን እንደሚመሰል ከቀረበ በኃላ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል፡፡
የባለድርሻ አካላት፣ የተባባሪ ድርጅቶች እና የመንግስትን ድጋፍና ጥረት በማጎልበት ከዘርፉ የሚጠበቀውን ጥራት ያለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና እውን በማድረግ በተለይም ወጣቱ በሥራ ዕድል ፈጠራና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለሀገሪቱ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋጋር እንደሚቻል ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ 1ሺህ 500 የሚጠጉ የግልና የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት እንደሚገኙ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ጉባዔው"ክህሎትን ማጎልበት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት" በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 22 የተጀመረ ሲሆን እስከ ሐምሌ 24/2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።